Follow Us:

የመጅሊስ ጠቅላላ ጉባዔ ህጋዊ አካሔድን ተከትሎ የተደረሠውን ውሳኔ እንደግፋለን::

የኢትዮጵያ ሙስሊም ተቋም መጅሊስ ባለቤትነት ጥያቄ ላለፈው ስርዓት መውደቅ ድምፃችን ይሰማ ቀዳሚ ፋና ወጊ መሆኑ ይታወቃል። ከለውጡ ወዲህ የሙስሊሙን ተቋም እንዲያሻግሩ፣ ህገ ደንቡን እንዲያፀድቁና ነጻና ገለልተኛ ምርጫ እንዲያካሂዱ አደራ የተረከቡ አባቶችና ምሁራን ከብዙ ዉጣ ወረድ በሗላ ህገ ደንቡ ፀድቆ ግዘያዊ ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት በመመረጡ በድር ኢትዮጵያ ከፍተኛ ደስታውን ለመግለጽ ይወዳል። ይህንን ታሪካዊ ስብስብ ልዩ የሚያደርገው ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልል የተውጣጡ ኡለሞች፣ ምሁራንና ሞያተኞች እንዲሁም የሙስሊሙ ማህበረሰብና የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በሂደቱ በመካፈልና በመምራት የፈፀሙት የሚያኮራ ተግባር መሆኑን በድጋሚ መግለጽ እንወዳለን።

በአሜሪካና ካናዳ የሚግኙ አጠቃላይ የበድር ኮሚኒቲዎችና አመራሮች ይህ የፀደቀው የመጅሊስ ህገደንብ፣ የስብሰባው ሂደት: የተመረጡት ፕሬዝዳንትና ምክትላቸው እንዲሁም ሁሉም የምክር ቤቱ አባላትና ቦርዱ የተመረጡበት ሂደት ዲሞክራሲያዊና አካታች መሆኑና ህጋዊ አሰራርን የተከተለ ሙሉ ተቀባይነት ያለው አካል መሆኑን እናምናለን። መንግስትም ሆነ ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ከዚሁ አካል ጋር ብቻ ሕጋዊ ግኑኝነት እንዲያደርጉ ለማሳሰብም እንወዳለን።

በድር ኢትዮጵያ ይህ እርምጃ ህዝበ ሙስሊሙ ነፃና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በማድረግ የመጅሊስ ተወካዮቹን ለመምረጥና ተቋሙን መልሶ ለመገንባት የመጀመሪያ እርምጃ እንጂ የመጨረሻ አለመሆኑን ያምናል። ጊዜያዊ ተመራጮችም ካለፈው በመማር ሁሉንም የኢትዮጵያ ሙስሊም ያለምንም ልዩነትና ግልጽነት በተሞላበት አሰራር በማሳተፍ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ነፃና ገለልተኛ ምርጫ በማድረግ ስልጣኑን ለተመራጮች እንደሚያስረክቡ ሙሉ እምነት አለን። መንግስትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አስፈጻሚ አካላት ሂደቱ የተሳለጠ እንዲሆን የበኩላቸውን እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። ሙስሊሙ ማህበረሰብም ኢስላማዊ ጨዋነትን በተላበሰና እርጋታ በተሞላበት በጥንቃቄ እንዲከታተል አደራ ማለት እንወዳለን።

በሌላ በኩል በዚህ ፍፁም ሰላማዊ ሂደት ያልተደሰቱና የሙስሊሞች አንድነት እረፍት የነሳቸው ከኢትዮጲያዊ ጨዋነት ባፈነገጠ መልኩ ለሺ ዓመታት የዘለቀውን የእምነት መከባበር የሚንዱ አንዳንድ ሰባኪያንና ሚዲያዎች በህብረተሰቡ መካከል አለመተማመን በመፍጠር ላይ ይገኛሉ። በተለይ ኢትዮ – 360 የሚባል የዩቲዩብ ሚዲያ ከሚዲያ ስነምግባር በፈነገጠ፣ ፈጽሞ ሚዛናዊነትና ሃላፊነት በጎደለው መልኩ በተከታታይ በሰራው ዘገባ በጎንደር ሙስሊሞች ላይ የደረሠውን ጭፍጨፋ ገዳዮችን በማጀገንና የተጎጂዎችን ድምጽ በማፈን፣ የጎንደሩን ተከትሎ በስልጤ ዞን ወራቤ የተከሰተውን ከልክ ባለፈ በማጋነንና የስልጤ ማህበረሠብ ያደረገውን በጎ ተግባር ወደ ጎን በመተው እንዲሁም የመጅሊሱን ፍፁም ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ወይይትና የኃላፊነት ሽግሽግ በ”መፈንቅለ መጅሊስ” በመፈረጅ የሄዱበተ ርቀት አሳፋሪ ነው። በድር ኢትዮጵያ በዚህ አጋጣሚ ኢትዮ – 360ና መሰል የሀይማኖት ካባ ለብሰው የሚንቀሳቀሱ ሚዲያዎች ከተመሳሳይ ድርጊት እንዲቆጠቡ በጥብቅ ያሳስባል። በአንፃሩ ሁሉንም ዜጋ በእኩልነት አይተው ሚዛናዊ ዘገባ የሚያቀርቡና የሙያ ግዴታቸው እየተወጡ ያሉ ሚዲያዎችን ከልብ ማመስገን እንወዳለን::

ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ሊገነዘብ የሚገባው በድር ኢትዮጵያ ማንኛውም ሙስሊምም ሆነ ኡለማዖች ከዚህ ሂደት ሊገለሉ አንደማይገባ ጽኑ እምነት አለው። ጠቅላላው ጉባዔው ለቀድሞው መጅሊስ ፕረዝዳንትና ምክትላቸው ያላቸውን እውቀትና ልምድ ከግንዛቤ በማስገባት በኢስላም ከፍተኛ ደረጃ በሚሠጠው የፈትዋ ዋና ሃላፊ አድርጎ መምረጡ የሚያስመሰግን ነው:: በተጨማሪም አሁን የተደረሠበትን ስምምነት ከፊት ሁነው እየመሩ እያስተባበሩ የነበሩ አባቶች በመጨረሻው ሰዓት ላይ ደርሰው ስብስቡን እውቅና መንፈግም ሆነ ስም ማጠልሸት ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በድጋሚ ለማሳሰብ እንወዳለን።

በመጨረሻም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሊያውቅ የሚገባው ሙስሊሙ አሁን የደረሠበት ደረጃ በማንም ችሮታ ሳይሆን በጋራ ባደረገው መራርና ሰላማዊ ትግል ብቻና ብቻ መሆኑን ማስታወስ ያስፈለጋል። ወደፊትም ሊገጥሙን የሚችሉ ፈተናዎች ወይም ወደሗላ ሊመልሰን የሚመጣን ማንኛውንም አካል በፍጹም ሰላማዊና ህግን በተከተለ መልኩ ለመታገል ዝግጁ መሆን ይጠበቅብናል። ባለፉት ጥቂት ወራት መንግስት በት/ቤት፣ በጎንደር ጭፍጨፋና በአ/አ ኢድ ሰላት ሁከት አያያዝ ሙስሊሙን ክፉኛ አሳዝኗል። ሆኖም አሁን ሙስሊሙ ማህበረስብ ህጋዊ መጅሊስ ለማቋቋም ቁርጠኛ መሆኑን መንግስት ተገንዝቦ ቀና ትብብር የሚያሳይበት ይህ ወሳኝ ግዜ መሆኑን እናምናለን:: ስለዚህ ይህ ሂደት በጥቂት ግለስቦች የስልጣን ጥማት ወይም ሀገሪቷ እንዳትረጋጋ አጀንዳ ባላችው አንዳድ አስፈጻሚ አካላት እንዳይጨናገፍ መንግስት ከወዲሁ ከፍተኛ ጥረትና ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል እንላለን። አላህ(ሱ.ው) ሀገራችንን ኢትዮጵያ ይጠብቅልን:: በድር ኢትዮጵያ 05/28/2022 

Share This:

Leave Your Comments

Your email address will not be published. Required fields are marked *

EMAS Copyright© 2022 | Made by AddisWay